ማንም ፡ ሳይነግርህ ፡ ሁሉን ፡ ብታውቅም፣
በልቤ ፡ ያለውን ፡ ከአንተ ፡ አልደብቅም።
ማንም ፡ ሳይጠቁምህ ፡ ሁሉን ፡ ብታይም፣
የውስጤን ፡ እኔን ፡ ከአንተ ፡ አልሰውርም።
ያየኸውን ፡ አሳይሃለሁ፤
ያወቅኸውን ፡ እነግርሃለሁ፤
ሸክሜ ፡ የሚቀለው ፡ ከእግርህ ፡ በታች ፡ ነው፤
ለአንተ ፡ ያሳየሁት ፡ ሁሉ ፡ መላ ፡ አለው፤
ላዬ ፡ ዝም ፡ ብሎ ፡ ውስጤ ፡ ግን ፡ ሲዋትት፣
ማንም ፡ ልብ ፡ እማይለው ፡ በሹክሹክታ ፡ ዐይነት፣ የውስጤን ፡ በውስጤ ፡ ነግሬህ ፡ በብርቱ፣
ሁሉ ፡ ደኅና ፡ ሆነ ፡ ሲደርስ ፡ ሰዓቱ።
ለአንተ ፡ ስነግር ፡ ይቀለኛል፤
ከአንተ ፡ መማከር ፡ ይቀናኛል፤
ከአኔ ፡ እኩል ፡ አታይ ፡ የሕይወቴን ፡ ክስተት፣
ሁሉ ፡ ራቁት ፡ ነው፤ ግልጽ ፡ ነው ፡ በአንተ ፡ ፊት።
እያየኸው ፡ አሳይሃለሁ፤
ያወቅከው ፡ እነግርሃለሁ፤
ሸክሜ ፡ የሚቀለው ፡ ከእግርህ ፡ በታች ፡ ነው፤
ለአንተ ፡ የሰጠሁት ፡ ሁሉ ፡ መውጫ ፡ አለው።
ፊትህ ፡ እሆናለሁ ፡ የሆንሁትን፣
ጭንብል ፡ አላጠልቅ ፡ ማስመሰልን፣
ቀድሞም ፡ ዐይንህ ፡ ቃላቴን ፡ ዘልቆ፣
ይመረምራል ፡ የልቤን ፡ ጠልቆ።
የጓዳዬ ፡ ምስጢረኛዬ
የምትሰማኝ ‘ምታደምጠኝ
‘ምትረዳኝ፣ ‘ምትረዳኝ።
ነገሬን ፡ እግርህስር ፡ አምጥቼ ፡ እጥላለሁ
ላንተ ፡ የነገርኩ ፡ እለት ፡ ፈውሴን ፡ አገኛለሁ።
የማላሳይህ፣ የማላዋይህ፣
‘ማላማክርህ፣ የማልነግርህ
ጉዳይ ፡ አለኝ ፡ ወይ?
የልቤ ፡ አምላክ ፡ ሆይ፤ ቅሩብ ፡ ለነፍሴ፣
ምን ፡ ነገር ፡ አለ ፡ የማስቀረው ፡ ብዬ ፡ በራሴ? (*2)