፪ኛ ፡ የጴጥሮስ ፡ መልእክት - ምዕራፍ ፫ (1st Peter - Chapter 3)
|
፩፡ እንዲሁም ፥ እናንተ ፡ ሚስቶች ፡ ሆይ ፥ ከባሎቻችሁ ፡ አንዳንዱ ፡ ለትምህርት ፡ የማይታዘዙ ፡ ቢኖሩ ፥ በፍርሃት ፡ ያለውን ፡ ንጹሑን ፡ ኑሮአችሁን ፡ እየተመለከቱ ፡ ያለ ፡ ትምህርት ፡ በሚስቶቻቸው ፡ ኑሮ ፡ እንዲገኙ ፡ ተገዙላቸው። ፪፡ ለእናንተም ፡ ጠጕርን ፡ በመሸረብና ፡ ወርቅን ፡ በማንጠልጠል ፡ ወይም ፡ ልብስን ፡ በመጎናጸፍ ፡ በውጭ ፡ የሆነ ፡ ሽልማት ፡ አይሁንላችሁ ፥ ፫፡ ነገር ፡ ግን ፡ በእግዚአብሔር ፡ ፊት ፡ ዋጋው ፡ እጅግ ፡ የከበረ ፡ የዋህና ፡ ዝግተኛ ፡ መንፈስ ፡ ያለውን ፡ የማይጠፋውን ፡ ልብስ ፡ ለብሶ ፡ የተሰወረ ፡ የልብ ፡ ሰው ፡ ይሁንላችሁ። ፬፡ እንዲህ ፡ በቀድሞ ፡ ዘመን ፡ በእግዚአብሔር ፡ ተስፋ ፡ ያደረጉት ፡ ቅዱሳት ፡ ሴቶች ፡ ደግሞ ፡ ለባሎቻቸው ፡ ሲገዙ ፡ ተሸልመው ፡ ነበርና ፤ ፭፡ እንዲሁም ፡ ሣራ ፡ ለአብርሃም። ጌታ ፡ ብላ ፡ እየጠራችው ፡ ታዘዘችለት ፤ እናንተም ፡ ከሚያስደነግጥ ፡ ነገር ፡ አንዳች ፡ እንኳ ፡ ሳትፈሩ ፡ መልካም ፡ ብታደርጉ ፡ ልጆችዋ ፡ ናችሁ። ፮፡ እንዲሁም ፥ እናንተ ፡ ባሎች ፡ ሆይ ፥ ደካማ ፡ ፍጥረት ፡ ስለ ፡ ሆኑ ፡ ከሚስቶቻችሁ ፡ ጋር ፡ በማስተዋል ፡ አብራችሁ ፡ ኑሩ ፤ ጸሎታችሁ ፡ እንዳይከለከል ፡ አብረው ፡ ደግሞ ፡ የሕይወትን ፡ ጸጋ ፡ እንደሚወርሱ ፡ አድርጋችሁ ፡ አክብሩአቸው። ፯፡ በመጨረሻው ፡ ሁላችሁ ፡ በአንድ ፡ ልብ ፡ ሁኑ ፥ የሌላው ፡ መከራ ፡ ለእናንተ ፡ እንደሚሆን ፡ አድርጉ ፥ እንደወንድሞች ፡ ተዋደዱ ፥ ርኅሩኆችና ፡ ትሑታን ፡ ሁኑ ፤ ፰፡ ክፉን ፡ በክፉ ፡ ፈንታ ፡ ወይም ፡ ስድብን ፡ በስድብ ፡ ፈንታ ፡ አትመልሱ ፡ በዚህ ፡ ፈንታ ፡ ባርኩ ፡ እንጂ ፥ በረከትን ፡ ልትወርሱ ፡ ለዚህ ፡ ተጠርታችኋልና። ፱፡ ሕይወትን ፡ ሊወድ ፡ መልካሞችንም ፡ ቀኖች ፡ ሊያይ ፡ የሚፈልግ ፡ ሰው ፥ መላሱን ፡ ከክፉ ፡ ከንፈሮቹንም ፡ ተንኰልን ፡ ከመናገር ፡ ይከልክል ፤ ፲፡ ከክፉ ፡ ፈቀቅ ፡ ይበል ፥ መልካምንም ፡ ያድርግ ፥ ሰላምን ፡ ይሻ ፡ ይከተለውም ፤ ፲፩፡ የጌታ ፡ ዓይኖች ፡ ወደ ፡ ጻድቃን ፡ ናቸውና ፥ ጆሮዎቹም ፡ ለጸሎታቸው ፡ ተከፍተዋል ፥ የጌታ ፡ ፊት ፡ ግን ፡ ክፉ ፡ ነገርን ፡ በሚያደርጉ ፡ ላይ ፡ ነው። ፲፪፡ በጎንም ፡ ለማድረግ ፡ ብትቀኑ ፡ የሚያስጨንቃችሁ ፡ ማን ፡ ነው ? ፲፫፡ ነገር ፡ ግን ፡ ስለ ፡ ጽድቅ ፡ እንኳ ፡ መከራን ፡ ብትቀበሉ ፡ ብፁዓን ፡ ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም ፡ አትፍሩ ፡ አትናወጡም ፥ ፲፬፡ ዳሩ ፡ ግን ፡ ጌታን ፡ እርሱም ፡ ክርስቶስ ፡ በልባችሁ ፡ ቀድሱት። በእናንተ ፡ ስላለ ፡ ተስፋ ፡ ምክንያትን ፡ ለሚጠይቁዋችሁ ፡ ሁሉ ፡ መልስ ፡ ለመስጠት ፡ ዘወትር ፡ የተዘጋጃችሁ ፡ ሁኑ ፥ ነገር ፡ ግን ፡ በየዋህነትና ፡ በፍርሃት ፡ ይሁን። ፲፭፡ በክርስቶስ ፡ ያለውን ፡ መልካሙን ፡ ኑሮአችሁን ፡ የሚሳደቡ ፡ ሰዎች ፡ ክፉን ፡ እንደምታደርጉ ፡ በሚያሙበት ፡ ነገር ፡ እንዲያፍሩ ፡ በጎ ፡ ሕሊና ፡ ይኑራችሁ። ፲፮፡ የእግዚአብሔር ፡ ፈቃድ ፡ እንዲህ ፡ ቢሆን ፥ ክፉ ፡ ስለ ፡ ማድረግ ፡ ሳይሆን ፡ በጎ ፡ ስለ ፡ ማድረግ ፡ መከራን ፡ ብትቀበሉ ፡ ይሻላችኋልና። ፲፯፡ ክርስቶስ ፡ ደግሞ ፡ ወደ ፡ እግዚአብሔር ፡ እንዲያቀርበን ፡ እርሱ ፡ ጻድቅ ፡ ሆኖ ፡ ስለ ፡ ዓመፀኞች ፡ አንድ ፡ ጊዜ ፡ በኃጢአት ፡ ምክንያት ፡ ሞቶአልና ፤ በሥጋ ፡ ሞተ ፡ በመንፈስ ፡ ግን ፡ ሕያው ፡ ሆነ ፥ ፲፰፡ በእርሱም ፡ ደግሞ ፡ ሄዶ ፡ በወኅኒ ፡ ለነበሩ ፡ ነፍሳት ፡ ሰበከላቸው ፤ ፲፱፡ ጥቂቶች ፡ ማለት ፡ ስምንት ፡ ነፍስ ፡ በውኃ ፡ የዳኑበት ፡ መርከብ ፡ ሲዘጋጅ ፥ የእግዚአብሔር ፡ ትዕግሥት ፡ በኖኅ ፡ ዘመን ፡ በቈየ ፡ ጊዜ ፡ ቀድሞ ፡ አልታዘዙም። ፳፡ ይህም ፡ ውኃ ፡ ደግሞ ፡ ማለት ፡ ጥምቅት ፡ ምሳሌው ፡ ሆኖ ፡ አሁን ፡ ያድነናል ፥ የሰውነትን ፡ እድፍ ፡ ማስወገድ ፡ አይደለም ፥ ለእግዚአብሔር ፡ የበጎ ፡ ሕሊና ፡ ልመና ፡ ነው ፡ እንጂ ፥ ይህም ፡ በኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ፡ ትንሣኤ ፡ ነው ፤ ፳፩፡ እርሱም ፡ መላእክትና ፡ ሥልጣናት ፡ ኃይላትም ፡ ከተገዙለት ፡ በኋላ ፡ ወደ ፡ ሰማይ ፡ ሄዶ ፡ በእግዚአብሔር ፡ ቀኝ ፡ አለ።
|