፪ኛ ፡ የጴጥሮስ ፡ መልእክት - ምዕራፍ ፪ (1st Peter - Chapter 2)
|
፩፡ እንግዲህ ፡ ክፋትን ፡ ሁሉ ፡ ተንኰልንም ፡ ሁሉ ፡ ግብዝነትንም ፡ ቅንዓትንም ፡ ሐሜትንም ፡ ሁሉ ፡ አስወግዳችሁ ፥ ፪፡ ጌታ ፡ ቸር ፡ መሆኑን ፡ ቀምሳችሁ ፡ እንደ ፡ ሆነ ፥ ለመዳን ፡ በእርሱ ፡ እንድታድጉ ፡ አሁን ፡ እንደ ፡ ተወለዱ ፡ ሕፃናት ፡ ተንኰል ፡ የሌለበትን ፡ የቃልን ፡ ወተት ፡ ተመኙ። ፫፡ በሰውም ፡ ወደ ፡ ተጣለ ፡ በእግዚአብሔር ፡ ዘንድ ፡ ግን ፡ ወደ ፡ ተመረጠና ፡ ክቡር ፡ ወደ ፡ ሆነው ፡ ወደ ፡ ሕያው ፡ ድንጋይ ፡ ወደ ፡ እርሱ ፡ እየቀረባችሁ ፥ ፬፡ እናንተ ፡ ደግሞ ፡ እንደ ፡ ሕያዋን ፡ ድንጋዮች ፡ ሆናችሁ ፥ በኢየሱስ ፡ ክርስቶስ ፡ ለእግዚአብሔር ፡ ደስ ፡ የሚያሰኝ ፡ መንፈሳዊ ፡ መሥዋዕትን ፡ ታቀርቡ ፡ ዘንድ ፡ ቅዱሳን ፡ ካህናት ፡ እንድትሆኑ ፡ መንፈሳዊ ፡ ቤት ፡ ለመሆን ፡ ተሠሩ። ፭፡ በመጽሐፍ። እነሆ ፥ የተመረጠና ፡ የከበረን ፡ የማዕዘን ፡ ራስ ፡ ድንጋይ ፡ በጽዮን ፡ አኖራለሁ ፡ በእርሱም ፡ የሚያምን ፡ አያፍርም ፡ ተብሎ ፡ ተጽፎአልና። ፮፡ እንግዲህ ፡ ክብሩ ፡ ለእናንተ ፡ ለምታምኑት ፡ ነው ፤ ለማያምኑ ፡ ግን ፡ አናጢዎች ፡ የጣሉት ፡ ድንጋይ ፡ እርሱ ፡ የማዕዘን ፡ ራስ ፡ የዕንቅፋትም ፡ ድንጋይ ፡ የማሰናከያም ፡ ዓለት ፡ ሆነ ፤ ፯፡ የማያምኑ ፡ ስለ ፡ ሆኑ ፡ በቃሉ ፡ ይሰናከሉበታልና ፤ ለዚህ ፡ ደግሞ ፡ የተመደቡ ፡ ናቸው። ፰፡ እናንተ ፡ ግን ፡ ከጨለማ ፡ ወደሚደነቅ ፡ ብርሃኑ ፡ የጠራችሁን ፡ የእርሱን ፡ በጎነት ፡ እንድትናገሩ ፡ የተመረጠ ፡ ትውልድ ፥ የንጉሥ ፡ ካህናት ፥ ቅዱስ ፡ ሕዝብ ፥ ለርስቱ ፡ የተለየ ፡ ወገን ፡ ናችሁ ፤ ፱፡ እናንተ ፡ ቀድሞ ፡ ወገን ፡ አልነበራችሁም ፡ አሁን ፡ ግን ፡ የእግዚአብሔር ፡ ወገን ፡ ናችሁ ፤ እናንተ ፡ ምሕረት ፡ ያገኛችሁ ፡ አልነበራችሁም ፡ አሁን ፡ ግን ፡ ምሕረትን ፡ አግኝታችኋል። ፲፡ ወዳጆች ፡ ሆይ ፥ ነፍስን ፡ ከሚዋጋ ፡ ሥጋዊ ፡ ምኞት ፡ ትርቁ ፡ ዘንድ ፡ እንግዶችና ፡ መጻተኞች ፡ እንደ ፡ መሆናችሁ ፡ እለምናችኋለሁ ፤ ፲፩፡ ስለሚመለከቱት ፡ ስለ ፡ መልካም ፡ ሥራችሁ ፥ ክፉ ፡ እንደምታደርጉ ፡ በዚያ ፡ እናንተን ፡ በሚያሙበት ፡ ነገር ፥ በሚጎበኝበት ፡ ቀን ፡ እግዚአብሔርን ፡ ያከብሩት ፡ ዘንድ ፡ በአሕዛብ ፡ መካከል ፡ ኑሮአችሁ ፡ መልካም ፡ ይሁን። ፲፪፡ ስለ ፡ ጌታ ፡ ብላችሁ ፡ ለሰው ፡ ሥርዓት ፡ ሁሉ ፡ ተገዙ ፤ ለንጉሥም ፡ ቢሆን ፥ ከሁሉ ፡ በላይ ፡ ነውና ፤ ፲፫፡ ለመኳንንትም ፡ ቢሆን ፥ ክፉ ፡ የሚያደርጉትን ፡ ለመቅጣት ፡ በጎም ፡ የሚያደርጉትን ፡ ለማመስገን ፡ ከእርሱ ፡ ተልከዋልና ፡ ተገዙ። ፲፬፡ በጎ ፡ እያደረጋችሁ ፥ የማያውቁትን ፡ ሞኞች ፡ ዝም ፡ ታሰኙ ፡ ዘንድ ፡ እንዲህ ፡ የእግዚአብሔር ፡ ፈቃድ ፡ ነውና ፤ ፲፭፡ አርነት ፡ ወጥታችሁ ፡ እንደ ፡ እግዚአብሔር ፡ ባሪያዎች ፡ ሁኑ ፡ እንጂ ፡ ያ ፡ አርነት ፡ ለክፋት ፡ መሸፈኛ ፡ እንዲሆን ፡ አታድርጉ። ፲፮፡ ሁሉን ፡ አክብሩ ፥ ወንድሞችን ፡ ውደዱ ፥ እግዚአብሔርን ፡ ፍሩ ፥ ንጉሥን ፡ አክብሩ። ፲፯፡ ሎሌዎች ፡ ሆይ ፥ ለበጎዎችና ፡ ለገሮች ፡ ጌቶቻችሁ ፡ ብቻ ፡ ሳይሆን ፡ ለጠማሞች ፡ ደግሞ ፡ በፍርሃት ፡ ሁሉ ፡ ተገዙ። ፲፰፡ በግፍ ፡ መከራን ፡ የሚቀበል ፡ ሰው ፡ እግዚአብሔርን ፡ እያሰበ ፡ ኃዘንን ፡ ቢታገሥ ፡ ምስጋና ፡ ይገባዋልና። ፲፱፡ ኃጢአት ፡ አድርጋችሁ ፡ ስትጎሰሙ ፡ ብትታገሡ ፥ ምን ፡ ክብር ፡ አለበት ? ነገር ፡ ግን ፡ መልካም ፡ አድርጋችሁ ፡ መከራን ፡ ስትቀበሉ ፡ ብትታገሡ ፥ ይህ ፡ ነገር ፡ በእግዚአብሔር ፡ ዘንድ ፡ ምስጋና ፡ ይገባዋል። ፳፡ የተጠራችሁለት ፡ ለዚህ ፡ ነውና ፤ ክርስቶስ ፡ ደግሞ ፡ ፍለጋውን ፡ እንድትከተሉ ፡ ምሳሌ ፡ ትቶላችሁ ፡ ስለ ፡ እናንተ ፡ መከራን ፡ ተቀብሎአልና። ፳፩፡ እርሱም ፡ ኃጢአት ፡ አላደረገም ፥ ተንኰልም ፡ በአፉ ፡ አልተገኘበትም ፤ ፳፪፡ ሲሰድቡት ፡ መልሶ ፡ አልተሳደበም ፡ መከራንም ፡ ሲቀበል ፡ አልዛተም ፥ ነገር ፡ ግን ፡ በጽድቅ ፡ ለሚፈርደው ፡ ራሱን ፡ አሳልፎ ፡ ሰጠ ፤ ፳፫፡ ለኃጢአት ፡ ሞተን ፡ ለጽድቅ ፡ እንድንኖር ፥ እርሱ ፡ ራሱ ፡ በሥጋው ፡ ኃጢአታችንን ፡ በእንጨት ፡ ላይ ፡ ተሸከመ ፤ (በግዕዝ ፡ እንዲህ ፡ ተጽፎአል። ወበእንተ ፡ ኃጣውኢነ ፡ ውእቱ ፡ ተሰቅለ ፡ ዲበ ፡ ዕፅ ፡ በሥጋሁ ፡ ከመ ፡ ያውፅአነ ፡ እምኃጣውኢነ ፡ ወበጽድቁ ፡ ያሕይወነ። ) ፳፬፡ በመገረፉ ፡ ቁስል ፡ ተፈወሳችሁ። እንደ ፡ በጎች ፡ ትቅበዘበዙ ፡ ነበርና ፥ አሁን ፡ ግን ፡ ወደ ፡ ነፍሳችሁ ፡ እረኛና ፡ ጠባቂ ፡ ተመልሳችኋል።
|